በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በክቡር ዶ/ር ዓብይ አህመድ መሪነት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ የዘንድሮ ችግኝ ተከላ ዕቅድ ከባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ብልጫ ያለው ሲሆን ይህም የአካባቢ መራቆትን ለመዋጋት እና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ ያለመ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ በ2016 የምርት ዘመን የአረንጓዴ ሌጋሲ ኢኒሼቲቭ በአገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ማቀዷ ይታወሳል።
በዚህ መርሃ ግብር መሰረት ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በመላው አገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘው 600 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር የመትከል ጥሪን ተከትሎ በአቡጃ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ የሚያገለግሉ ሠራተኞችና የሠራተኞች ቤተሰብ በተሳተፉበት ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡
ይህም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሁሉም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሚሲዮኖች ፕሮጋራሙ ዕቅድ ተይዞ ችግኝ ተከላው አገራችን በብሄራዊ ደረጃ ከያዘችዉ መርሃ ግብር ጋር በአንድ ወቅት ችግኝ ተከላዉን በማካሄድ ለቀሪዉ አለም አርአያ እንዲሆን የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ተሰርቷል።
ይህ የአገራችን አረንጓዴ ሌጋሲ ኢኒሼቲቭ ከጎረቤት አገሮች አልፎ ለመላው አፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ በአርአያነት መምራቷን ስትቀጥል እ.ኤ.አ. በ2019 በከቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ መሪነት የተጀመረው ይህ ኢኒሼቲቭ በመላ ሀገሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎችን በመትከል የአካባቢ መራቆትን እና የደን መጨፍጨፍን ለመከላከል ያለመ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በአረንጓዴው ሌጋሲ ኢኒሼቲቭ ዓለም አቀፋዊ የፀረ-አየር ንብረት ለውጥ የተስፋ ብርሃን ሆናለች። ኢትዮጵያ በደን መልሶ የማልማት ቁርጠኝነት የከባቢ መራቆት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን ለቀሪው አለም በዘላቂ ልማትና በከባቢ ጥበቃ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ባለፉት አምስት አመታት አስደናቂ የሆነ 40 ቢሊየን ችግኞችን በመላ ሀገሪቱ ተክላለች። ይህ ሰፊ የደን መልሶ ማልማት ስራ የተራቆቱ የመሬት ገጽታዎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ተፅእኖ በመቅረፍ እና የሀገሪቱን የበለፀገ የብዝሀ ሕይወት ሀብት በመጠበቅ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ቁርጠኝነት ያሳየችው ኢትዮጵያ ባለፈው አመት በአንድ ቀን 566 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የአለም ክብረ ወሰን አስመዝግባለች። ይህ ያልተለመደ ስኬት ኢትዮጵያ ለአካባቢ ጥበቃ ያላትን ቁርጠኝነት ከማጉላት ባለፈ ዓለም አቀፍ ትኩረትን እና የደን መልሶ ማልማት ጥረቷን ለዓለም ያስመስከረችበት ሆኗል።